Jump to content

User:Abayneh Reda

From Wikipedia, the free encyclopedia

“በሃይማኖት ቀልድ የለም” ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ

“የተጭበረበርንበት ዘመን አከተመ” የወልቂጤ ሕዝብ

በፀረ ሐራጥቃ ተጋድሎው ሒደት እጅግ ወሳኝ እና በድል ያሸበረቀ ጉባኤ በወልቂጤ ተካሔደ፡፡ ውሉደ ሐራጥቃ ወልቂጤን እንደ አንድ ምሽግ አድርገው ይቆጥሯት ነበረ፡፡ እንደ ድንጋይ ግንብ የመመኪያ አጥር አድርገውት የነበረው “ቄስ ነኝ” ባይ ድራሹ ከጠፋ ሰነበተ፡፡ ምነዋ? ያላችሁ እንደኾን ጀግናውና በሃይማኖት ጉዳይ ድርድር የማያውቁት ቆራጡ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ቅጥሩን አፈራረሱታ! የጵጵስና ሥራቸውን አሐዱ ብለው የጀመሩት በዕቅበተ እምነት ላይ አትኩረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዘመናዊ ዘረኝነት ታጥሮ የትውልድ ቦታዬ ነው የሚነካኝ የለም ብሎ ይታጀር የነበረውን ተሸናፊን “ወግድ በቤታችን እንዳንተ ያለ ሐራጥቃ አይቀልድም ብለው በባዶው ምንም ሳይኖረው ከተኮፈሰበት ማማ ከመሬት አውርደው ደባለቁት፡፡ ከዚያች ወዲህ ዝር ብሎ አያውቅም፡፡ ጀግና ብቅ ሲል ማን ከፊቱ ይቆማል!

የወልቂጤ ቅድስት ማርያም ሰንበት ት/ቤት የተመሠረተበትን ፴፱ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከዐርብ ታኅሣስ ፳-፳፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. የተካሔደው ዐቢይ ጉባኤ የወልቂጤን ሕዝብ ሃይማኖታዊ ወገንተኛነት በአደባባይ ያረጋጋጠ ነበር፡፡ የሰንበት ት/ቤት አባላት ላደረጋችሁልን የፍቅር መስተንግዶ ምስጋና ይድረሳችሁ፡፡ እናንተ ስትበረቱ ብዙ የጠላት ቅጥሮች ይደረመሳሉ፡፡ ራሳችሁን እየጠበቃችሁ በሃይማኖት እያነጻችሁ ዘመኑን እየዋጃችሁ ለቤተ ክርስቲያን መወገንን ገንዘብ አድርጉ፡፡ በቅድስት ማርያም ዐውደ ምሕረት በአቡነ ቀሌምንጦስ ቸልተኝነት የሐራጥቃ አድራሽ ፈረሶች ብዙ ዘልለውበታል፡፡ ዝላያቸው መረን የለቀቀ ስለነበር ሕዝቡ አንገቱን ደፍቶ ይኖር እንዳልነበር ዛሬ ቀና ብሎ ለሃይማኖቱ የመደራደሪያ ክፍተት እንደሌለው ዐሳይቷል፡፡ ከእነ እገሌ በቀር ማንም ድርሽ አይልም ይባል የነበረበት ዘመን ዛሬ ታሪክ ኾኗል፡፡

በእኛ ዕድሜ የቤተ ክርስቲያናችን ፈርጥ ከኾኑት ባለታሪኮች መካከል አንዱ የኾነው በኵረ መዘምራን ኪነ ጥበብ ወልደ ቂርቆስ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ከመምጣቱ አስቀድሞ በዚህች የወልቂጤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቀድሶ አድጎባታል፡፡ ከኹለት ዓመት በፊት ግን እዚያ መድረክ ላይ ማይክ ቀምተው ከመድረክ እንዲወርድ አድርገውት ነበረ፡፡ ከ፵ ዓመታት በላይ እናት ቤተ ክርስቲያኑን ያገለገለውን ታላቁን ወንድማችንን እንዲህ ሲገፈታትሩት ያዩ አረጋውያን እንባቸውን ረጭተው ለፈጣሪ አመልክተው በኃዘን ተጠብሰው አንጀታቸው ቅጥል እያለ ከራርመዋል፡፡ ለያሬዳዊ ዜማ እነርሱ ስፍራ የላቸውማ! ስንኳን ለዜማው ለሃይማኖቱም ግድ አልሰጣቸው፡፡ እርሱም እንባውን አፍስሶ ከመድረኩ ተሰናብቶ እንዳልነበር ዛሬ ግን በክብር ቀና ብሎ የቤተ ክርስቲያን ልጅነቱን በተገፋበት መድረክ መልሶ አረጋግጧል፡፡ ገፍታሪዎቹ ግን ዛሬ የሉም፡፡

በዚህ ጉባኤ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በበታው ተገኝተው ጉባኤውን እየመሩ ፍጻሜው እንደ ጅማሬው ያማረ እንዲኾን ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ አባቶቻችን ጰጳሳት አሁን ነገሩን በያዙበት ሁኔታ ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ እነርሱ ከመድረኩ በራቁ ቁጥር ዐውደ ምሕረቱ ይደፈራል፣ ውርውር የሚሉት ይነግሡበታል፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳን በአርባ ምንጭ፣ በባሕርዳርና በወልድያ ዛሬ ደግሞ በወልቂጤ በብፁዓን አበው ጉባኤዎች ሲመሩ ውጤታቸው እንዴት የሰመረ እንደሚኾን ዐይተናል፡፡ ወልቂጤ ይህንን ትመሰክራለች፡፡

አንዳንድ ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን ከሚገባቸው በላይ አሳቢ ኾነው እየቀረቡ ሕዝቡ እውነተኛውን መንገድ እንዳያውቅ እንቅፋት ይኾናሉ፡፡ በአጥቢያቸው ወይም በሀገረ ስብከታቸው ስማቸው የገነኑ ሐራጥቃዎች ባሉበት እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዳይመጡ በጥበብ ለተቃራኒው ቡድን ይጫወታሉ፡፡ ዋናው መንገዳቸው አባቶችን ቀርበው ማሸበር ነው፡፡ “እነ እገሌ ከመጡ እዚህ ያሉት ሰዎች ተወላጆች ስለኾኑ ሕዝቡን ያስነሱብዎታል፤ ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም አይበጅም” ይላሉ፡፡ ነገሩን በውል የተረዱት አባቶች እንዲህ ሲወሥኑ ግን ሕዝቡ ከማን ጋር እንዳለ ይረጋገጣል፡፡ ስንኳን በአባቶች ላይ ሊነሣ በደረሰበት መከራ ቁጭቱን እየገለጠ የአባቶቹ አጋር መኾኑን አስመሰከረ፡፡ ያ ሁሉ ወሬ ዛሬ የለም፡፡ ዲላና ይርጋ ዓለም ላይ ክንብንባቸው ይህ ነበር፡፡ ሐዋሳ ላይ ማሸበሪያቸው እንዲህ ነበር፡፡ ወልቂጤ ላይ ደግሞ ይብሳል፡፡ ዛሬ ግን እርሱም አልፏል፣ ማለት እንደ ጉም ተንኗል፣ እንደ አመድ ተበትኗል፡፡

በዚህ ጉባኤ ላይ በኵረ መዘምራን ኪነ ጥበብ፣ ሊቀ ሊቃውንት ስሙር፣ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ፣ መምህር በላይ ወርቁ፣ መምህር አካለ ወልድ፣ ወንድማችን ዘውዱ እና ዘማሪ ታሪኩ ታድመውበታል፡፡ ሐራጥቃ ራስ ራሱን ተቀጥቅጦበታል፡፡ በጉባኤው መጠናቀቂያ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ “በሃይማኖት እና በዐይን ቀልድ የለም” በማለት ጠንካራውን የቤተ ክርስቲያን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ማዕዳችን ላይ ዐይነ ምድሩን ልጣል የሚል ቢኖር ማን ይታገሳል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ማዕዳችን ናት፡፡ እንበላባታለን፣ እንጠጣባታለን፡፡ አልደረስንባቸውም፣ አትድረሱብን ማለት ይገባል፡፡ በነፃነታቸው እንደፈለጉ መኾን ይችላሉ፡፡ የፈለጉትን ቢያምኑ የሚከለክላቸው የለም፡፡ ነገር ግን ከአጥራችን ውጭ ብቻ መኾኑን አስረግጠን እንነግራቸዋለን፡፡ የሰው ጥላቻ የለብንም፣ በትክክሉ እንመለሳለን ብለው ከመጡ ከልባቸው መኾኑን አረጋግጠን በቀኖናው መሠረት እንቀበላቸዋለን ሲሉም አባታዊ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በእጅ ጽሑፍ በወረቀት ተጽፎ የተሰጠኝ አንድ መልእክት እንዲህ ይላል፡- እንደዚህ ያለው የቤተ ክርስቲያናችን ድምጽ ትዝታ ኾኖብን ነበር፡፡ ዛሬ ግን ድሮ ካቆምንበት እንቀጥል ዘንድ ሕይወት ዘርታችሁበታል፡፡ ደጋግማችሁ አስተምሩን፡፡ በደማችን ውስጥ እንደ ካርቦን ሞኖክሳይድ የተሠራጨው መርዝ እስኪወጣ ድረስ አስለቅቁልን፡፡ ማንነታችንን ከነጠቁን ሰዎች ፈልቅቃችሁ መልሱልን፡፡

በተሸናፊ የሚመራው የሐራጥቃ አድራሽ ፈረሶች መንጋ በወልቂጤ ላይ አከርካሪው ተሰብሯል፡፡ ሕዝቡ አማራጭ ስላልነበረው እንጅ መምህራኑን ያውቃል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ከእነማን ወገን እንዳለ በተግባር በድምጽ በማያቋርጥ የጋለ ጭብጨባ አረጋግጧል፡፡ እናም የተጭበረበርንበት ዘመን አከተመ ብሎ የሐራጥቃ አድራሽ ፈረሶችን ሽኝት አድርጎላቸዋል፡፡